2005 ዓ.ም
እለት ተዕለት እየጨመረ ከቁጥጥር ውጪ ለመውጣት እየዳዳ የነበረውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር ገበያው ላይ የተበተነውን ገንዘብ መሰብሰብ በአንድ በኩል ከፊል አላማው ያደረገ፣ በሌላም በኩል ከጊዜ ወደ ጊዜ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለከፍተኛ ምሬት በመዳረግ ፖለቲካዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት በመንግስት ላይ ያሳደረውን የመኖሪያ ቤት ዕጥረት ለማርገብ በማሰብ መንግስት አንድ መላ ነደፈ፤ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ ለመጣል፡፡በዚህም መሰረት ከዚያ ቀደም በ1997 ዓ.ም. በብላሽ ያደረገውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ በድጋሚ ምዝገባ ስም በተወሰነ ወርሀዊ መዋጮ ህብረተሰቡ እንዲመዘገብ ከማድረግ ባለፈ አዳዲስ ተመዝጋቢዎችን በማካተት በሶስት አይነት መንገድ ማለትም በ40/60፣ 20/80 እና 10/90 ተመዝግበው፣ በመቆጠብ በሂደት በዕጣው የቤት ባለቤት መሆን እንደሚችሉ በማሳወቅ መዘገበ፤ ገንዘቡንም ሰበሰበ፡፡
በወቅቱ ይህ በብዙኀኑ የከተማ ነዋሪዎች እንደ ትልቅ ዕድል የታየውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ምዝገባ ለማካሄድ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኮንስትራክሽንና ቤቶች ልማት ቢሮ የቤቶች ልማት አስተዳደር ኤጀንሲ የቤት ፈላጊዎች ለምዝገባ ሲመጡ ማሟላት የሚገባቸዉን ቅድመ ሁኔታና የምዝገባ አፈፃፀም ስርዓትን በተመለከተ መመሪያ አወጣ፡፡ የቤት ፈላጊዎች ምዝገባው ‘ግልጽና ፍትሃዊ እንዲሆን በማድረግ የከተማዋ ነዋሪዎች በመንግስት በተቀረጹት የቤት ልማት ፕሮግራሞች ተጠቃሚ የሚሆኑበት እድል እንዲመቻችና ፍትሃዊ የሆነ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ’ አላማ እንዳደረገ የሚናገረው መመሪያው ተመዝጋቢዎች በዚህ የጋራ መኖሪያ ቤት ተጠቃሚ ለመሆን ሊያሟሉት ይገባል ያለውን 3 ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀምጧል፤ እድሜ ከ18 አመት በላይ የሆነ ፣ በከተማዋ ቢያንስ ለሁለት ተከታታይ አመታት የኖረ ወይም ለሁለት ተከታታይ አመታት በስራ ወይም በትምህርት ምክንያት ከከተማዋ ውጪ የኖረበትን ህጋዊ ማስረጃ ማቅረብ የሚችልና ማስረጃው በቦታው ለምን ያህል ጊዜ እንደቆየ ወይም እንደሚቆይ በዝርዝር ማስረጃ ማቅረብ መቻል እንዳለበት በግልፅ ደነገገ፡፡
ይህንንም ተከትሎ ነዋሪው በየአቅሙ እንዲመዘገብ ተብሎ ከቀረቡት ሶስት አማራጮች ውስጥ የሆነው የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ምዝገባ ከተመዝጋቢው በሚጠየቀው ከፍ ያለ ተቀማጭ እንዲሁም በመንግስት በኩል በተገለፀው የተሻለ የጥራት ደረጃ ባለቤትነት ምክንያት የሚመራበት ራሱን የቻለ መመሪያ በማስፈለጉ የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ የ40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች ልማት ፕሮግራም የቅድሚያ አወሳሰንና የቤት ማስተላለፍ ስርዓት አፈጻጸም መመሪያ ቁጥር 21/2005 ዓ.ም የሚል መመሪያ አወጣ፡፡
በመመሪያው መሰረት የ40/60 የጋራ መኖሪያ ቤት ተመዝጋቢ የብድር ተጠቃሚ ለመሆን ቢያንስ 40% ቁጠባውን ማሟላት ያለበት ቢሆንም ለብድር ብቁ ከሆኑ ደንበኞች መካከል የመኖሪያ ቤቱን ዋጋ 100% ተቀማጭ ቅድሚያ ያደረጉ ቅድሚያ እንደሚያገኙ ይደነግጋል፡፡ ይህንን ተከትሎ በዚህ መደብ ከተመዘገቡ 160,000 ነዋሪዎች መካከል ከአስራ ሶስት ሺህ ያላነሱ ተመዝጋቢዎች በመመሪያው መሰረት የቅድሚያ ዕጣ ውስጥ ለመግባት የሚያስችላቸውን 100% በመጀመሪያው የምዝገባ ዕለት በማስገባት የቤት ባለቤት ለመሆን በጉጉት መጠባበቅን ‘ሀ’ ብለው ጀመሩ፡፡
ይሁን እንጂ በአጭር ጊዜ የቤት ባለቤት የመሆን ተስፋ ሰንቆ የቆጠበው ነዋሪ የመጀመሪያውን የቤት ማስተላለፍ እጣ ውስጥ ለመግባት 4 ድፍን አመታትን ለመጠበቅ ተገደደ፡፡ ያበደርኩት ገንዘብ ያልተሸራረፈ እና ጉድለት የሌለበት በመሆኑ ለደንበኞቼም ማስተላለፍ ያለብኝ ምንም ጉድለት የሌለባቸው ቤቶች መሆን አለባቸው በማለት ለመዘግየቱ እንደ ምክንያት የሰጠው የኢትዮጲያ ንግድ ባንክ በክራውን እና ሰንጋተራ ሳይት ያሉ 1292 መኖሪያ ቤቶችን በመጋቢት ወር 2009 ዓ.ም. የሳይት ቅኝት በማድረግ በመመሪያው መሰረት 100% ለቆጠቡ የመጀመሪያ ዙር ‘እድለኞች’ እጅግ ዘግይቶም ቢሆን አስተላለፈ፡፡