ፍትሕ ለአዲስ አበባ ህዝባዊ ዘመቻ እንዲፈጠር ያስቻሉ ገፊ ምክንያቶች

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ስርዓቱ ከመሳተፍ እና ወሳኝ ከመሆን ተገልለዉ፤ በከተማቸዉ ሀብት ላይ ዉሳኔ ሰጪ እንዳይሆኑ ስርዓታዊ ጫና ሲደረግባቸዉ ቆይቷል፡፡ ይህ ጫና የመስተዳድሩ አወቃቀር ላይ ትልቅ ተጽንኦ ያሳደረ በመሆኑ መስተዳድሩ እና በተለያዩ ግዜያት ለከተማዋ የሚሾሙት አስተዳዳሪዎች እምብዛም የአዲስ አበቤዎችን መሰረታዊ የኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ጥያቄዎች ምላሽና መፍትሔዎችን ሲሰጡ አይስተዋልም፡፡ በዚህም ሳቢያ አዲስ አበቤዉ በገዛ ከተማዉ ባይተዋር ሲሆን ይታያል፡፡  የእለት ተእለት ህይወቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ዉሳኔዎች ላይ እንኳን ተሳታፊ ባለመሆኑ ከመፍትሔ ይልቅ ችግሮቹን ተላምዶ እንዲኖር ይገደዳል፡፡

አዲስ አበቤዎች ካሉባቸዉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መካከል የመኖሪያ ቤት፣ የመጠጥ ዉሃ እና የመብራት ሀይል አቅርቦት፣ የመንገድ፣ የጤና ፣ የትራንስፖርት አገልግሎት፣ የወጣቶች ስራ አጥነት እና ህዝቡን እያስመረረ የሚገኘዉ የኑሮ ዉድነት ተጠቃሾች ናቸዉ፡፡ ከህዝብ ቁጥር መጨመር ጋር የመኖሪያ ቤት ፍላጎቱም በዛዉ ልክ የጨመረ ሲሆን፤ ከ 1997 ዓ.ም ወዲህ አነስተኛ ገቢ ያለዉን አዲስ አበቤ የቤት ባለቤት ለማድረግ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ( ኮንዶሚኒየም) ፕሮጀክት በመንግስት ተቀርጾ ተግባራዊ ለማድረግ ተሞክራል፡፡ ነገርግን የጋራ መኖሪያ ቤቶች የታለመላቸዉን አላማ ስተዉ አዲስ አበቤዉን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ፤ አስተዳዳሪዎች እና በየደረጃዉ ያሉ የመንግስት ኃላፊዎች በትዉዉቅ እና የአንድ ቡድን ወይም ብሔር ወገን የሆኑ ግሎሰቦችን ወይም ቡድኖችን ተጠቃሚ ሲያደርጉበት ይስተዋላል፡፡

አዲስ አበቤዉ ለዓመታት የቤት ባለቤት ለመሆን ያለመታከት ከሚያገኛት ላይ እየቆጠበ እየተጠባበቀ ቢገኝም ከህልም እንጀራነት ግን ሊያልፍ አልቻለም፡፡ በተለይም ከ 2010 ዓ.ም ወዲህ ችግሩ ከመቼዉም ግዜ በላይ ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ሌላዉ የአዲስ አበቤዉን ምሬት የሚያባብስ ድርጊት ደግሞ የመሬት ወረራ ነዉ፡፡ የህዝብ ሀብት የሆነዉ መሬት አዲስ አበባ ላይ በጠራራ ፀሐይ ይወረራል፡፡ ይህ ህገ-ወጥነት በመንግስት መዋቅር ዉስጥ ባሉ አካላት ጭምር የተደገፈ መሆኑን ማስረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ነገርግን በህገ-ወጥ ተግባር ላይ የተሳተፉ ግለሰቦችም ሆነ የመንግስት አካላት ለፈጸሙት ጥፋት ተጠያቂ ሲሆኑ አይስተዋልም፡፡ ይልቁንም የአንድ ሰሞን መነጋገሪያ ከመሆን አያልፍም፡፡

እነዚህ መድሎዎች ነዋሪዎችን በእጅጉ ከማስቆጣታቸዉም ባለፈ እሮሮዉን የሚያስተጋባለት የሌለዉ አዲስ አበቤ ከ መንግስት ጋር ሆድና ጀርባ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ በመሆኑም ከላይ የተነሱት በደሎች ማለትም ኢፍትሐዊ የመኖሪያ ቤት ክፍፍል፣ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና ተጠያቂነት የሌለበት አድሏዊ አሰራር ለ #ፍትህለአዲስአበባ ዘመቻ ገፊ ምክንያቶች ናቸዉ፡፡ ይህ ዘመቻም አዲስ አበቤዉ ላይ ለተፈጸሙት በደሎች ፍትህን ይጠይቃል፡፡ የሰፊዉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እሮሮ እና ቅሬታዎች በጋራ መኖሪያ ቤቶች እና መሬታ ወረራዎች ብቻ የተገደቡ ባለመሆናቸዉ ሌሎች የአዲስ አበቤዉ የተዳፈኑ ጩኸቶች ሰሚ እንዲያገኙ ድምፅ ይሆናል፡፡

የ ፍትሕ ለአዲስ አበባ ዘመቻ አዘጋጆች በደልን የሚጠየፉ፣ ኢ-ፍትሐዊነትን የሚቃወሙ በአዲስ አበባ ላይ የሚፈጸሙ ማናቸዉም አይነት ህገ-ወጥ ድርጊቶች የሚያሳስባቸዉ፣ የከተማዋ እና የነዋሪዎቿ የወደፊት ዕጣ ፈንታ የሚያስጨንቃቸዉ፤ የዜግነት ግዴታቸዉን ለመወጣት ተስፋን ያነገቡ በማህበራዊ ሚዲያዎች አማካኝነት የተገናኙ ከከተማዋ አብራክ የወጡ የአዲስ አበባ ወጣቶች ስብስብ ነዉ፡፡

የዘመቻው አላማ ትኩረቱን በአዲስ አበባ ከተማ እና ነዋሪዎቿ ላይ በማድረግ ከተማዋና አዲስ አበቤዉ በኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ዘርፎች የሚደርሱባቸዉን አድሏዊ አሰራሮች እና በደሎች ነቅሶ በማዉጣት መፍትሔ እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል፡፡ የአብዛኛዉ አዲስ አበቤ ጥያቄዎች የሆኑትን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢ-ፍትሐዊ ዕደላ እና ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ እንዲቆም የሚመለከታቸዉን የመንግስት አካላት በተደራጀ መልኩ ይጠይቃል፡፡  የተወሰዱ እርምጃዎችን ተከታትሎ ለህብረተሰቡ ያሳዉቃል፡፡ በተፈጸሙ ኢ-ፍትሐዊ እና ህገ-ወጥ ድርጊቶች ዙሪያ አስቸኳይ ምርመራ አንዲደረግ፣ በህገ-ወጥ ድርጊቶች ላይ ተሳታፊ የሆኑ ግለሰቦችም ይሁኑ ቡድኖች ተጠያቂ እንዲሆኑ እና ፍትሕ እንዲሰፍን ዘመቻዎችን ያካሂዳል፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በእለት ተዕለት ኑሯቸዉ ዉስጥ የሚገጥሟቸዉን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሳንካዎች በመለየት መፍትሔ እንዲያገኙ ይጥራል፡፡ #ፍትሕለአዲስአበባ ዘመቻ የህብረተሰቡ የተዳፈኑ ድምጾች የሚሰሙበት መድረክ እንዲሆን ያደርጋል ፡፡

ፍትሕ ለአዲስ አበባ ዘመቻ የከተማ መስተዳድሩ በተዋረድ ከከንቲባ ጽ/ቤት እስከ ወረዳ መዋቅር ድረስ የሚያሳልፋቸዉን ዉሳኔዎች፣ የሚተገብራቸዉን አሰራሮች፣ የሚያወጣቸዉን ዝርዝር እቅዶች እና አፈጻጸሞች፤ ደንብ እና መመሪያዎች ግልጽነት የታከለባቸዉ እና ተጠያቂነት የሰፈነባቸዉ እንዲሆኑ ጥረት ያደርጋል፡፡

ፍትሕ ለአዲስ አበባ ዘመቻ አዲስ አበቤዉ በዙሪያዉ እየተከናወኑ ያሉ ጉዳዮችን በትኩረት እንዲቃኝ፤ በጥልቀት እንዲያጤን ይመክራል፡፡ ነዋሪዉ በራሱ ከተማ ባይተዋር ከመሆን ይልቅ እኩል ተጠቃሚ አንዲሆን እና በከተማዋ ጉዳዮች ላይ ይመለከተኛል የሚል አዲስ አበቤ እንዲፈጠር የማንቃት ዘመቻዎችን ያካሂዳል፡፡

ራዕያችን በአዲስ አበቤያዊ ስነ-ልቦና የተዋቀረ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ፍላጎት የሚያስጠብቅ፣ በከተማዉ ጉዳይ ላይ ጠያቂ እና ምክንያታዊ ትዉልድ እንዲፈጠር የሚያግዝ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸዉ ዋስትና የሚያገኝበት ፍትሐዊ መደላድል እንዲኖር የሚሰራ፣ አዲስ አበቤዉ መብትና ግዴታዉን አዉቆ አንዲንቀሳቀስ የሚያስተባብር፣ በከተማዋም ይሁን በፌደራላዊ የመንግስት መዋቅሮች ዉስጥ አዲስ አበቤዉ እዉነተኛ ተወካይ እንዲኖረዉ የሚያስችል፣ በማናቸዉም ከተማዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሌሎች የሀገሬዉ ወንድም እና እህት ህዝቦች ጋር እኩል ተሳትፎ እንዲኖረዉ የሚተጋ፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለከተማቸዉ እና ለሀገራቸዉ እድገት የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ፣ መንግስታት እና አስተዳዳሪዎች ቢቀያየሩም ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የአዲስ አበቤዉ አለኝታ የሆነ ተቋማዊ አሰራር የተዘረጋበት፤ ከብሔርተኝነት፣ ሐይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ነጻ የሆነ የሲቪክ ማህበር ማቋቋም፡፡

ህልማችን ለነዋሪዎቿ እና ለሚመርጧት ሁሉ ምቹ የሆነች፤ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቷ የተረጋገጠባት ህብረ-ብሔራዊት አዲስ አበባን ማየት፡፡

 

 

Related Posts