የዛሬ አበባዎች የነገ ……… ?

‹‹የዛሬ አበባዎች፤ የነገ ፍሬዎች…..›› እነዚህ ተረት የመግቢያ ሰላምታዎች ዓመታት ተሻግረንም በሀሳባችን ዉልብ ሲሉ ያ ጣፋጭ የልጅነታችንን ዘመን ያስታዉሱናል፡፡ አስታዉሰዉ ልጅነታችንን ያስናፍቁናል፡፡ ዘወትር እሁድ ጠዋት ካልጋችን ተነስተን ከእድሜ እኩያ ጓደኞቻችን ጋር በቤት ዉስጥ ተሰብስበን ሳምንቱን ሙሉ ቡጉጉት የምንጠብቃቸዉን ‹‹የልጆች አባት›› የሆኑትን ‹‹አባባ ተስፋዬ››ን ያ ጣፋጭ ተረታቸዉን ለማዳመጥ እጃችንን ለሳላምታ እያዉለበለብን እንቀበላቸዋለን፡፡ እሳቸዉም ፍቅራቸዉን ሳይሰስቱ እየለገሱን፤ በተረታቸዉ እያዋዙ ‹‹ የዛሬ አበቦች፤ የነገ ፍሬዎች…..›› እያሉ ነገን በተስፋ ያስመለክቱናል፡፡ የወላጅን ክብር፤ የሀገር ፍቅርን ያስተምሩናል፡፡

የመጀመሪያዉ የትምህርት ቀን ሲጀምር የቀሰምነዉን የሀገር ፍቅር በተግባር ለማሳየት እንሽቀዳደማለን፡፡ በረድፍ በረድፍ በመሆን የሠንደቅ ዓላማችንን ከፍታ ተከትለን ወደ ሰማይ ሽቅብ እያንጋጠጥን በስሜት ብሔራዊ መዝሙር እንዘምራለን፡፡

 

 

የዜግነት ፡ ክብር ፡ በኢትዮጵያችን ፡ ጸንቶ ፣

ታየ ፡ ሕዝባዊነት ፡ ዳር ፡ እስከዳር ፡ በርቶ ።

ለሰላም ፡ ለፍትሕ ፡ ለሕዝቦች ፡ ነጻነት ፣

በእኩልነት ፡ በፍቅር ፡ ቆመናል ፡ ባንድነት ።

መሠረተ ፡ ጽኑ ፡ ሰብእናን ፡ ያልሻርን ፣

ሕዝቦች ፡ ነን ፡ ለሥራ ፡ በሥራ ፡ የኖርን ።

ድንቅ ፡ የባህል ፡ መድረክ ፡ ያኩሪ ፡ ቅርስ ፡ ባለቤት ፣

የተፈጥሮ ፡ ጸጋ ፡ የጀግና ፡ ሕዝብ ፡ እናት ።

እንጠብቅሻለን ፡ አለብን ፡ አደራ ፣

ኢትዮጵያችን ፡ ኑሪ ፡ እኛም ፡ ባንቺ ፡ እንኩራ ።

ፍቅር እና ተስፋ!

በስርዓተ-ትምህርቱ ዉስጥ የተካተተዉ  ‹‹ሥነ-ዜጋ እና ሥነ-ምግባር›› የትምህርት ዓይነት የዜጎችን ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ ግዴታዎች ፣ መንግስት ፣ ህዝብ፣ አስተዳደር፣ህገ-መንግስት ወዘተ… ስለሚባሉ መርሆች አስተዋወቀን፡፡ አነዚህ ዲሞክራሲያዊ መርሆች ግን ከትምህርት ክፍል የንድፈ ሀሳብ እዉቀት ተሸግረዉ በገሀድ ሲነገሩ የሰማነዉ በ 1997 ዓ.ም የምርጫ ዋዜማ ሰሞን ነዉ፡፡ ከተማችን አዲስ አበባ አንድ ትልቅ ሀገራዊ ኹነት ለማዘጋጀት ደፋ ቀና ትላለች፡፡ አዋቂዉ፣ ወጣቱ፣ ሚዲያዉ ሁሉ በዚህ ብዙም በማይገባን ወሬ ተጠምዷል፡፡ ልጆች ነንና እምብዛም ተሳትፎ አናደርግም፡፡ ነገርግን በትምህርት ክፍል ዉስጥ በቁንጽልም ቢሆን ያወቅናቸዉን ሀሳቦች በተግባር ለማየት እድሉን ያገኘን መስሎ ስለተሰማን፣ ሁኔታዉ በሙሉ ቀልባችንን ይገዛዉ ጀመር፡፡ የዛሬ አበቦች ነገን ፍሬያማ ለማድረግ እንዲችሉ እነዚህ ጉዳዮች መሰረታዊ ናቸዉ፡፡ ዳሩ ግን ከ 1997ቱ ምርጫ በኋላ ነገር ዓለሙ ሁሉ ተቀያየረ፡፡ ከተማችን አዲስ አበባም በፖለቲካ ወጀብ ትናጥ ገባች፡፡ የ ‹‹ነገ ፍሬዎቿን››ም ትገብር ያዘች፡፡ ትኩሳቱ መማሪያ ቅጥር ግቢያችን በመድረስ በተማሪ ጩኸት እየታጀበ የትምህርት ገበታችንን ማሰናከሉን ተያያዘዉ፡፡ ወላጆቻችንም የማስጠንቀቂያ መዓት ያዥጎደጉዳሉ፡፡”ዋ አቡሽ! ንብ የሚል ቃል ከ አፍህ እንዳይወጣ”…..”አንቺ ልጅ ሁለት ጣትሽን አንዳታዉጪ! ” ሌላም…ሌላም፡፡  እኛም ንብን ከማር ሳይሆን ከ ፖለቲካ ፓርቲ ፤

ሰማያዊን ከቀለም ሳይሆን ከ ፌደራል ፖሊስ ልብስ ጋር አያይዘን በልጅነት ልቦናችን አስፍረን ቀረን፡፡

በድህረ 1997 አዲስ አበባ መልኳን ቀየረች፡፡ መንግስትና ህዝብ ሆድና ጀርባ ሆኑ፡፡  የከተማችን አስተዳደር በየግዜዉ የሚያሳልፋቸዉ ዉሳኔዎች የከተማዉን ህዝብ ለምሬት ዳረገ፡፡ የመልካም አስተዳደር እጦት ተንሰራፋ፡፡ የኑሮ ዉድነቱ ታይቶ በማይታወቅ ልክ ናረ፡፡ ወጣቶች ስራ እና ተስፋ በማጣታቸዉ ለስደት ተዳረጉ፡፡ ከተማችን አዲስ አበባ ዉስጥ ነዋሪዎች ለዘመናት በአብሮነት የቀለሱት ድንኳን በ ‹‹ በመልሶ ልማት›› ሰበብ ፈረሰ፡፡ የከተማዋን ነዋሪ የመኖሪያ ቤት እጦት ለመቅረፍ ታስቦ የተጀመረዉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ፕሮጀክትም / ኮንዶሚኒየም ቤቶት/ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ ለኢህፍትሐዊ እደላ ተጋለጠ፡፡ ባጠቃላይ አዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿ ለበርካታ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ቀዉሶች ተዳረጉ፡፡ መታበስ ያልቻሉ እምባዎች ፈሰሱ፡፡

ባለቤት አልባ እየሆነች የመጣችዉ  አዲስ አበባ አመራሮቿን በግዜ ሂደት እየለዋወጠች ዛሬ ላይ ብትደርስም ለነዋሪዎቿ እዚህ ግባ የማይባል ጠቀሜታን መስጠት ተስኗታል፡፡ ችግሩ ዛሬም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ የትናንት ‹‹አበቦችም›› ዛሬ ላይ ደርሰዉ አለን ብንልም፤ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ችግሮችን ከመዉረስ በቀር የጓጓንለት እና በተለያዩ ተረቶች የተነገረን ፍሬያማ ህይወት ግን የዉሃ ሽታ ሆኖ ቀረ። ይህ ትዉልድ በ‹‹አጥፊ›› እና ‹‹በጠፊ›› አስተሳሰብ መሀል ኑሮን ተፍጨርጭሮ ለማሸነፍ እየሞከረ ያለ ትውልድ ነዉ። ምን እንኳን እንደሚረከብ በግልፅ ማወቅ አልቻለም።

በየግዜዉ በህብረተሰቡ ዉስጥ እየሰፋ የሚሄደዉ የኑሮ ደረጃ ልዩነት፣ ስራ ማጣት፣ ልቅ የሆነ ሙስና ፣ አድሏዊ እና ብልሹ አሰራር፣ የመኖሪያ ቤት እጦት ፣ የተለያዩ ሸቀጦች እና  አገልግሎቶች ዋጋ መጨመር ፣ የትራንስፖርት እጥረት ….ወዘተ ተዳምረዉ እንኳንስ የተመኘዉን ህይወት ሊያገኘዉ ቀርቶ ችግር የእለት ጉርሱን ሊያስጥለዉ እየደቆሰ ያጎብጠዋል፡፡ የአዲስ አበባ ወጣት ተስፋ እንደ ሰማይ መና ርቆታል፡፡

እነዚያ ፍሬያማ ህይወቶች ለየትኛዉ ትዉልድ ነዉ የሚደርሱት?

እኛ የአዲስ አበባ ወጣቶች ትናንት የተመኘነዉን ብሩህ ተስፋ ባንደርስበትም፤ ወጣቱ የሚጠይቀዉን መሠረታዊ ጥያቄዎች ግን ለሚመለከተዉ አካል ለማስተላለፍ ግን ደርሰናል፡፡ ‹‹ለምን?›› እንላለን፡፡ የዛሬዎቹ ‹‹አበቦችም›› የነጋቸዉን መልካም ፍሬ እንዲያመልጣቸዉ አንፈቅድም፡፡ ሀገራችንም ዛሬ ላይ ብዙ የደረሱ የትናንት አበቦች ስላሏት ምናልባት ለመልሱ ብዙ አንርቅ ይሆናል።

ቸሩን ያምጣልን!

#ፍትሕለአዲስአበባ

Related Posts