የተዳፈነዉ ጩኸት እና የአዲስ አበቤዉ ተስፋአልባ ጉዞ

የክረምት ወራት ተገባደዋል፤ ዝናቡ እና ነጎድጓድ በአዲስ አበባ ሰማይ ላይ እየተፈራረቁ ያለማንም ከልካይ እንዳሻቸዉ ሲምነሸነሹበት ከርመዋል፤ አሮጌዉ ዓመት ዘመኑን ጨርሶ አዲሱና ተስፈኛዉ ዓመት እስኪረከበዉ ድረስ ቆጥቦ ካስቀመጠልን የማለፊያ ወቅት ጷግሜ ላይ ደርሰናል፡፡ መስከረም በአደይ አበባ ታጅቦ ሊጠባ አለሁ አለሁ እያለ ነዉ፤ አዲስ አበባ የኔ ከተማ፣ የሁላችን መዲና በአደይ ስትታጀብ ልዩ ገጽታን ትላበሳለች፣ ትፈካለች፣ ትፍለቀለቃለች፤ ለነገሩ አዲስ አበባ የራሷ ቀለም፣ ስነ-ልቦና፣ የህብረተሰብ ዉቅር (Social Structure) ያላት ከተማ ናት፤ ህብረ-ብሔራዊነት መገለጫዋ የሆነ ዉብ ከተማ፡፡ማነህ?…ማነሽ? ከየት ነህ? ከየት ነሽ? ብላ ሳትጠይቅ ሁሉን በእኩል ሽር ጉድ ብላ የምታስተናግድ፣ የተለያዩ ማንነቶች፣ እምነቶች፣ አስተሳሰቦች ማዕከል የሆነች ኮዝሞፖሊታን መዲና ናት፡፡ አፈር ፈጭተን፤የዛሬን አያድርገዉና ሰፊ ሜዳዎቿ ላይ በማይረሱ የልጅነት ጨዋታዎች ቦርቀን፣ ተጣልተን ታርቀን፣በታሪካዊ መዝናኛዎቿ እሁዳችንን አሳምረን፣የጎረቤት ፍቅር ጠግበን ላደግን ልጆቿ ደግሞ አዲስአበባ በልባችን ልዩ ስፍራ አላት፤ በወርቅ ቀለም ልባችን ላይ ታትማ ትኖራለች፡፡

አዲስአበባ ክፉና ደጉን፣ጦርነቱን ድሉን፣ችግሩን፣ሀሴቱን፣መከራዉን፣ ተድላዉን ችላ የተለያዩ መንግስታትን እንዳመጣጣቸዉ ኖር! ብላ አስተናግዳ የዘመናዊነት መገለጫ እንደሆነች እነሆ 134 ዓመታትን አስቆጠረች፡፡ ወይ አዲስ አበባ ወይ አራዳ ሆይ! አዲስ አበባ አንቺ እኮ ልዩ ነሽ!

ፒያሣ፣ መርካቶ፣ ጉለሌ፣ ደጃች ዉቤ፣ 4ኪሎ፣ 6ኪሎ፣ ካዛንቺስ፣ ቀበና፣ አባ ኮራን፣ አዉቶብስ ተራ፣ መሳለሚያ፣ ጣልያን ሠፈር፣ ፈረንሣይ፣ ገዳም ሠፈር፣ ሠራተኛ ሠፈር፣
ጨርቆስ፣ ቄራ፣ ዳትሰን ሠፈር፣አዲሱ ገበያ፣ራስ ደስታ፣ ፍል ዉሃ፣ አዋሬ፣ ለገሃር፣ስታዲዮም፣ እሪ በከንቱ፣ ዶሮ ማነቂያ፣ ጦር ኃይሎች፣ ኮተቤ፣ መገናኛ፣ ኦልድ ኤርፖርት፣
ቦሌ (የቱን ጥዬ የቱን ላንሳ?) ያሉ ልጆችሽን ሠብስበሽ ኖረሻል፡፡

አዲስ አበባ ቤቴ፤ የምድር ሠገነቴ!

To be poor is to be invisible to your fellow human beings, and the indignity of invisibility is often worse than the lack of resources. Francis Fukuyama

 

አዲስ አበባዬ! ዛሬስ ክንዷ ዛለ መሰል ልጆቿን መሠብሠብ ተስኗታል፤ እርጅና ይሁን ድህነት፣ ድካም ይሁን ሀዘን፣ አቅም ማጣት ይሁን ተስፋ ማጣት እንጃ! ብቻ አዲስ አበባ ወዟ እየተሟጠጠ ይታየኛል፤ በዉስጧ ከቀሩት ልጆቿ ጋር በቤቷ ባይተዋር ሆናለች፤ ልብ ምቷ ሁሉ ተቀያይሯል፤ ስርዓቶች እየተቀያየሩ ሀብትና ንብረቷን የተለያዩ ታፔላዎችን እየለጠፉ መቀራመት ከጀመሩ ከራርመዋል፡፡ መጦሪያዋን ያለከልካይ ስትነጠቅ አይታ በህግ-አምላክ! ብላ ብትጮህ ሰሚ የለም! በቀረዘዘ ድምጿ ድረሱልኝ! ብትል ልጆቿ በልማት ተነሺ፣ በመሪ እቅድ፣ በመልሶ መልማት ወዘተ…ሰበብ ቀድመዉ ጥለዋት በመሄዳቸዉ ማን ያስጥላት! ቀሪዎቹም ቢሆን ህልዉናቸዉን ለመቀጠል በቻሉት መንገድ ሁሉ በባህርም በሰማይም መቼ እንደሚመለሱ እንኳን ሳያዉቁ በመሰደዳቸዉ ማን ይድረስላት! ለነገሩ ባገኙት አጋጣሚ በዝባዦቿም ይህን ደካማጎን አዉቀዉ አይደል እንዲህ የሚያደርጓት፡፡ አስተዳዳሪዎቿ ዉድ ሀብትና ንብረቷን መሀል ከተማ ላይ በመቶ ሚሊዮኖች ቀየሩት፤ ልጆቿን ወደ ዳር ገፍተዉ ተመልካች አድርገዉ እነሱ በፌሽታ ሰከሩ፤ ግፈኛ ግፍ ስለማይፈራ ነዉ ግፈኛ የተባለዉ፤ ስጋዋን በልተዉ አጥንቷን አስቀሩት፤ መቼም ሁሉም ይሄዳሉ እንዳመጣጣቸዉ፡፡ የቀረዉን አጥንትም በመንጋጋዉ ሊያደርግ ሲጠባበቅ የቆየሁ አያጅቦም የዋሁዋ ሸገር ወለል አድርጋ በከፈተችለት በራፍ ሰተት ብሎ ገብቶ የድርሻዉን አፈፍ፤ የችኩሉ አያጅቦ ታፔላ ደግሞ የተለየ ነዉ፤እንዳዉ ለወሬም አይመች፡፡ የአያቴ ነዉ፣ የአባቴ ነዉ፣ የኔ ነዉ፣ የጓደኛዬ ነዉ፣ ወዘተ…ብቻ አጃኢብ ነዉ፡፡ ‘ለኔ እናት የበጃት የለም ያም ‘አንጪ’ ያም ‘አንጪ’ ‘’ በማለት በግርምትም በንዴትም ትታዘባለች አዲስ አበባ፤ነገር አዋቂም አይደለች፡፡

ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ፤ በተለያዩ ግዜያት አዲስ አበባ ዉስጥ ስለተፈፀሙ መልከ ብዙ ግፎች፣ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራዎች፣ አግባብነት የሌለዉ የኮንዶሚንየም ዕደላ፣ ስለ መልካም አስተዳደር እጦት፣ ቅጥ ስላጣዉ ድህነት፣ የመሠረተ ልማት ችግሮች… ኸረ ብዙ ብዙ ተብሏል ወገኖቼ፡፡ ጉዳዩ የሚያሳስባቸዉ ዜጎችም በግለሰብም በቡድንም በመሆን ሰሚ የሌለዉ ጩኸት አሰምተዋል፡፡ በቅርቡም አብዛኞቻችን የምናዉቀዉን ህገ-ወጥነት በጥናት በተደገፈ ሠነድ ተመልክተን ተብከንክነናል፣ ተበሳጭተናል፣ ሆድም ብሶናል፤ ይባስ ብሎ የከተማዉ አስተዳደር አናት ላይ ተቀምጠዉ የነበሩ አሁንም የተተኩ አመራሮች ለተፈፀመዉ ድርጊት አንገት የሚያስደፋና ያገኛትን እየቆጠበ የቤት ባለቤት ለመሆን የቀረችዉን ከመርፌ ቀዳዳ የጠበበች ጭላንጭል ተስፋ ሙሉ በሙሉ የሚሳጣ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ጉድ አንድ ሰሞን ብቻ ሆኖ እንዳይቀር በማሰብ ችግሩ የሚያሳስበን ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያዉ ላይ ፍትህን የሚጠይቅ ዘመቻ አካሂደናል (ድምጻችንን የሚያሰሙ ተወካዮች በወረዳም ይሁን በምክርቤት እነማን እንደሆኑ እንኳን በዉል የማናቃቸዉ መሆኑን ልብ ይሏል)፡፡ ለመሆኑ ይህ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና ኢፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ የሚያስከትላቸዉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ ቀዉሶች ምንድናቸዉ? የፖለቲካ ቀዉሶችን የሚያስከትሉት የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ምስቅልቅሎች ድምር ዉጤት እንደሆኑ ታሳቢ በማድረግ የፖለቲካዉን ትንታኔ ለፖለቲከኞቹ በመተዉ በወፍ በረር እና አቅም በፈቀደዉ መጠን ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀዉሶች ላይ አተኩራለሁ፡፡ ተከተሉኝ!

የኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊ እ ናፖለቲካዊ ቀዉሶችን በ3 ደረጃዎች ከፋፍሎ የሚያሳይ ፒራሚድ

ኢኮኖሚያዊ ቀዉሶች

ከላይ ያለዉ የፒራሚድ ምስል እንደሚያሳየዉ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራዉና ኢፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዕደላ የሚያስከትሏቸዉ ቀዉሶች ሶስት ደረጃዎች አሉት፡፡ ከታች ሰፊዉን ቦታ የሚይዘዉ ኢኮኖሚያዊ ሲሆን ቀጥሎ በኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ አማካኝነት የሚፈጠረዉ የማህበራዊ ቀዉስ ነዉ፤ የሁለቱ ቀዉሶች ድምር ዉጤት ደግሞ የፖለቲካ ቀዉስ እንዲከሰት ያደርጋል፡፡ አንዱ መፍትሄ ያጣ ችግር ሌላ ክስተትን እየወለደ የሚሄድበት ሂደት (Domino effect) ይዘት አለዉ ሊባል ይችላል፡፡

ፍትሀዊነት ያልሰፈነበት አሰራር በዋናነት በግለሰቦች እንዲሁም በህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የኢኮኖሚ መዛባትን (Economic Inequality) ይፈጥራል፡፡ የመሬት ወረራ አካል ወይንም የኮንዶሚኒየም ቤቶች ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች የተሻለ የመኖሪያ ቤት የመገንባት፣ የመሸጥ የመለወጥ፣ በማከራየት ፣ንብረታቸዉን በማስያዣነት በማዋል የባንክ ብድር በማግኘት ሌሎች ሀብትና ንብረቶችን ማፍራት ይችላሉ፤ ከዚህም ባለፈ ሌሎች ሀብት ማግኛ መንገዶች ዉስጥ መሰማራት ያስችላቸዋል፡፡ ለምሳሌ፡ የንግድ ኢንቨስትመንት ዘርፍ ዉስጥ መግባት፣ፋብሪካዎችን መትከል፣ የኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶችን ያለ ተወዳዳሪ ማግኘት፣ ለወጪና ገቢ ንግዶች እጅግ አስፈላጊ የሆነዉን የዉጭ ምንዛሬ በቀላሉ ያለ ወረፋ ማግኘት፣ የባንክ አክሲዮኖችን መግዛት እና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ተጨማሪ ሀብት በማግኘታቸዉ የመግዛት አቅማቸዉ (Purchasing Power) ስለሚያድግ የተሻለ መኖሪያቤት፣ የጤና እና ትምህርት አገልግሎቶችን፣ የመሠረታዊ ፍጆታ አገልግሎትን ያለምንም ችግር በቀላሉ እንዲያገኙ ያስችላቸዋል፡፡ እነዚህ ዜጎች የሚያደርጓቸዉ እንቅስቃሴዎች ኢመደበኛ ስለሚሆኑ ገበያ በፍላጎት እና አቅርቦት (Demand & Supply) ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን ከፍተኛ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ይባስ ብሎም የእለት ገቢን እንዲሁም የወርሐዊ ገቢን ጠብቆ ለሚኖረዉ አብዛኛዉ የሕብረተሰብ ክፍል እንደ ምግብ፣ ትራንስፖርት፣ መኖሪያ ቤት፣ የጤና ፣ የትምህርት..ወዘት ያሉ መሠረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ዉድ ስለሚሆኑ በቀላሉ ለማግኘት ይቸገራል፡፡

አሁን ባለንበት ተጨባጭ የዕለት ጉርስን ለመሸፈን የሚታትረዉ እና የወር ደመዎዝን ጠብቆ የሚኖረዉ የህብረተሰብ ክፍል ትልቁ ወጪዉ የመኖሪያ ቤት ኪራይ ነዉ፡፡ የሚያገኘዉን ገቢ ለቤት ኪራይ ይከፍላል፣ የምግብ ወጪ ይጠብቀዋል፣ ቤተሰብ የመሰረተ እንደሆነ የትምህርት ቤት ክፍያን ጨምሮ ከልጆች ጋር የተያያዙ ወጪዎች ይጠብቁታል፣ የትራንስፖርት ወጪም አለ፣ የተቀረችዉን የገቢዉን እንጥፍጣፊ በተስፋ ለሚጓጓለት የኮንዶሚኒየም ቤት ይቆጥባታል፡፡ካልቻለም መቆጠቡን ይዘላል ወይንም እስከነ አካቴዉ ይተዋል፡፡ እንዲህ ባለ የህይወት ትንቅንቅ ዉስጥ ተሰንጎ ከተያዘ እና ማጣፊያ ካጠረዉ ቤተሠብ እነደነገሩ የተቆጠበን ገንዘብ ያለምንም ሀፍረት እና ማን አለብኝነት መቀማት እጥፍ ድርብ በደል ነዉ፡፡

የኑሮ ዉድነትን ያባብሳል፤ እንኳንስ ዘንቦብሽ እንዲያዉም ጤዛ ነሽ እንዲሉ አበዉ እንኳን እንዲህ አይነት ኢፍትሐዊነት ተጨምሮበት ለወትሮዉም እያናረ ያለዉ የኑሮ ዉድነት ላይ ነዳጅ ያርከፈክፋል፡፡ የአዲስአበባ ነዋሪ በተለይ ከ1997 ዓ.ም ወዲህ ባሉ ዓመታት ቅጥ ባጣ የኑሮ ዉድነት ፍም መለብለቡ በገሀድ የሚታወቅ ሀቅ ነዉ፡፡ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በየወቅቱ የሚያወጣቸዉ የዋጋ ግሽበት መረጃዎች ይህንኑ እዉነታ የሚያረጋግጡ ናቸዉ፡፡ ይህ እንዲሆን የሚፈረድበት ነዋሪ ረጅም ርቀትን አልሞ ከመኖር ይልቅ ምሬት ዉስጥ ሆኖ የጨለመዉ ሌሊት ንጋት ደጃፍ እስኪደርስ በቁጭት ይጠባበቃል፡፡ የተሻለ ገቢ ያላቸዉ፣ ከዉጭ በሚመጣ ድጋፍ የሚታገዙ፣ የተለያዩ የዉጭ ድርጅቶች እና መንግስታዊ ተቋማት በጥሩ ደመዎዝ የሚሰሩ ዜጎች በአንጻራዊነት የተሻለ ጫናዉን ሊቋቋሙት ቢችሉም አብዛኛዉ አነስተኛ ገቢ ያለዉ የህብረተሰብ ክፍል ግን ለተለያዩ ማህበራዊ ቀዉሶች ይዳረጋል፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤቶች የዕጣ አወጣጥ ኢፍትሐዊ ከመሆኑም በላይ ቆጥቦ የመኖሪያ ቤት እድሉ ተጠቃሚ ለሆነዉ ባለእድለኛ በግዜዉ ቤቶቹ ተጠናቀዉ ስለማይሰጡት የኮንስትራክሽን የማቴሪያል ዋጋ ጨምሯል በሚል ሰበብ ለተጨማሪ ወጪ እና እንግልት ይዳረጋል፡፡

ከላይ ያነሳናቸዉ ችግሮች ሲዳመሩ ከሀገሪቱ 50 በመቶ በላይ የሚሆነዉን የሀገር ዉስጥ የጥቅል ምርት(GDP) ላይ አስተዋጽኦ ያላት አዲስ አበባ ላይ መደበኛ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዉን በመጉዳት የከተማዋ ብሎም የአገሪቱ አጠቃላይ ኢኮኖሚ ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ቀጣዩን ክፍል ያንብቡ

Related Posts