የተዳፈነዉ ጩኸት እና የአዲስ አበቤዉ ተስፋአልባ ጉዞ ክፍል ሁለት

ቀደም ሲል በወፍ በረር የተመለከትናቸዉ መሠረታዊ የኢኮኖሚ ቀዉሶች መንግስት አስፈላጊዉን መፍትሄ እየሰጠ በግዜ መፈታት ካልተቻሉ ቀዉሶች ተባብሰዉ ማህበራዊ ምስቅልቅሎችን ይፈጥራሉ፡፡ በአንድ አገር ዉስጥ መፍትሄ ያጡ ማህበራዊ ስብራቶች ደግሞ መጠገን ወደማይችሉ ፖለቲካዊ ዉጥንቅጥ ያመራሉ፡፡

Daron Acemoglu & James A. Robinson

Nations fail when they have extractive economic institutions, supported by extractive political institutions that impede and even block economic growth

የተዛባ ኢኮኖሚ (Economic Inequality) የተንሰራፋበት ህብረተሰብ ዉስጥ የመደብ ልዩነት ይፈጥራል፤ ጥቂቶች ኢኮኖሚዉን ይቆጣጠራሉ፡፡ ፍትሀዊ የአሰራር ስርዓት ከመዘርጋት ይልቅ፣ ለጥቂቱ መብት የሚቆም ለብዙሀኑ ግድ የሌለዉ ስርዓት ይፈጥራል፡፡ ብዙሀኑ በተለይም አነስተኛ ገቢ ያለዉ የህብረተሰብ ክፍል ህገ-መንግስቱ ያጎናጸፈዉን ንብረት የማፍራት መብት እንኳን እንዳያስጠብቅ ያደርገዋል፡፡ በዚህ መሀል ለሚፈጸም በደል ፍትህ እንዳይረጋገጥ የፍትህ ስርዓቱ የጥቂቶች ፍላጎት ማስፈጸሚያ ይሆናል፡፤ ሌላ ማነቆ፡፡ ኢፍትሀዊነት በተንሰራፋበት ከተማ እና አገር ዉስጥ ዴሞክራሲን ማስፈን ከህልም እንጀራነት አያልፍም፡፡

የአዲስ አበባ ነዋሪ ለዓመታት የሚወክለዉን የህዝብ አመራር መምረጥ እና በፖለቲካዊ ሂደቱ ዉስጥ መወከል እና ተሳትፎ ማድረግ ባለመቻሉ የኢኮኖሚያዊ የዉሳኔ አቅሙን ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አጥቷል፡፡ በመሆኑም ነዋሪዉን የሚጎዱ ህገ-ወጥ የመሬት ወረራን እና ኢፍትሐዊ የኮንዶሚኒየም ቤት ዕደላ በሚካሄድበት ወቅት ድርጊቱን የሚቃወሙ ተቆርቋሪ ተወካዮች (የክፍለ ከተማም ይሁን የከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት) ባለመኖራቸዉ ሃይ ባይ ላጣ ብዝበዛ (Exploitation) ይዳረጋል፡፡

ለሁሉም ዜጎች እኩል የሆነ መደላደል በሌለበት ሁኔታ በህዝቦች ዘንድ በሚፈጠር የኢኮኖሚ ልዩነት አማካኝነት ገቢዉ አነስተኛ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል መሠረታዊ አገልግሎቶችን ማግኘት አይችልም፡፡ በዚህም ምክንያት የተለያዩ እርምጃዎችን ለመዉሰድ ይገደዳል፡፡ ለምሳሌ፡-ይኖሩበት ከነበረዉ የኪራይ ቤት በዋጋም በጥራትም የሚቀንስ ከአካባቢዉ ርቆ ያለ መኖሪያ ቤት ይከራያሉ፣ መሠረታዊ የምግብ ፍጆታዎችን ይዘት መቀየር አንዲሁም እለታዊ የመመገብ ብዛቱን መቀነስ፣ የልጆች ትምህርት ቤት ለመቀየር መገደድ ወዘተ የመሳሰሉት አይነት አስገዳጅ ሁኔታዎች ይፈጠራሉ፡፡ የምግብ ዋስትናዉ ያልተረጋገጠ (Food Insecurity) ፣ ደስተኛ እና ጤናማ ቤተሠብ እንዳይኖር ብሎም ቤተሰብ እስከመበተን ሊደርስ ይችላል፡፡

በመንግስት መዋቅር የተደገፈ የመሬት እና የቤት ልማት ዘረፋ እንዲከናወን ያስቻለበት አንዱና ቁልፉ ጉዳይ በየደረጃዉ መዋቅር ዉስጥ ከአመራሩ እስከ ህግ አስከባሪዉ ድረስ ያሉ አካላት የአዲስ አበባ ነዋሪ ያልሆኑ በትዉዉቅ አልያም ብሄር ተኮር ቅርርብ የተሸበቡ መሆናቸዉ ነዉ፡፡ የከተማዉ ወጣቶች ተወልደዉ ባደጉበት ከተማ ዉስጥ በሚገኙ የወረዳ እና የክፍለ ከተማ ቢሮዎች እንኳን ተቀጥረዉ የሚሰሩበት እድል አይፈጠርላቸዉም፡፡ የስራ ፈጠራ በሚል የሚታቀዱ ፕሮጀክቶች እና ገንዘቦች ለተቸገረዉ ወጣት ከመዋል ይልቅ በመሬት ወረራም ይሁን በኮንዲሚኒየም እደላዉ ወደ ከተማ ለሚገቡ አዲስ ነዋሪዎች የተመቻቹ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ሳቢያ የአዲስ አበባ ወጣቶች በስር አጥነት ይንገላታሉ፡፡ የተሻለ ስራ ለማግኘት ከሚረዱ መንገዶች አንዱ የተሻለ እና ጥራት ያለዉ ትምህርት ማግኘት ነዉ፡፡ አሁን ባለዉ ነባራዊ ሁኔታ የዕለት ኑሮዉን አሸንፎ ከማደር አልፎ ራስን ጥራት ባለዉ ትምህርት መደገፍ የማይይቀመስ ነዉ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ተስፋ ማጣት ወዴት ያመራል?

አንድ የአዲስ አበባ ወጣት በ 25 ዓመት ዕድሜዉ/ዋ በ 1997 ዓ.ም የኮንዶሚኒየም ዕጣ ላይ ቢመዘገብ/ብትመዘገብ እና እስካሁን እየቆጠበ የዕድሉ ተጠቃሚ ባይሆን/ ባትሆን ከ15 ዓመታት በኋላ የ 40 ዓመት ጎልማሣ ይሆናል/ትሆናለች፡፡ በአንጻሩ ምንም ጥበቃም ሆነ ቁጠባ ማድረግ ሳይጠበቅባቸዉ የቤት እድለኛ የሚሆኑ ዜጎችን ማየት የሚፈጥረዉን ስሜት ማሰብ አያዳግትም፡፡ ከዛም በኋላ በ 2005 ዓ.ም የተመዘገቡ ወጣቶችስ የሚሰማቸዉ ስሜት? መልሱን ለናንተዉ ልተዉ፡፡ የቀድሞ የአዲስ አበባ ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ እንዲሁም እሳቸዉን ተክተዉ የከንቲባነት ስልጣኑን የተረከቡት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በወቅታዊ የመሬት ወረራና የጋራ መኖሪያ ቤቶች ኢፍትሐዊ ዕደላ ዙሪያ የሠጡት አስገራሚ አስተያየት እጅግ ተስፋ አስቆራጭና አንገት የሚያስደፋ እንዲሁም መሪና ተመሪ ሆድና ጀርባ እንደሆኑ በግልጽ
የሚያሳይ ነዉ፡፡

ታድያ ወጣቶች በዚህ ሁኔታ በሀገራቸዉ እንዴት ተስፋ ሊኖራቸዉ ይችላል? ተስፋቸዉ የተሟጠጠ ወጣቶች ወደ ሥርቆት፣ ወንጀሎች (ግድያን ጨምሮ)፣ ሱስ ያመራሉ፤ ብሎም ህይወታቸዉ ላይ ፈርደዉ ስደትን ምርጫቸዉ ያደርጋሉ፡፡ ከስደት ተርፈዉ እና በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙ ዜጎችም የሚያገኙት ገቢ ኑሯቸዉን በአግባቡ እንዲመሩ ስለማያስችላቸዉ ኑሯቸዉን ለመደጎም ሲሉ ሳይወዱ ሙስና ዉስጥ ይዘፈቃሉ፡፡ በሙስና የሚተዳደር ዜጋ ማፍራት ደግሞ ለሀገር ዉድቀት ነዉ፡፡

በመንግስት መዋቅር የተደገፈ የመሬት ወረራና ኢፍትሐዊ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እደላ ከሚያስከትሉት ማህበራዊ ችግሮች መሀል ‘የነባር እና የመጤ’፤ ‘የወራሪ እና የተወራሪ’ ስሜት/አስተሳሰብ ያመጣል፤ በነዋሪዎች ዘንድም ያለመተማመንን/ መጠራጠር ይፈጥራል፡፡ ይህም የአዲስአበባ ነዋሪዎች የኖሩበትን እና የሚታወቁበትን ህብረብሔራዊ ስሜት እና የልቦና ዉቅር ይሸረሽራል፡፡ ለዘመናት የተገነባዉ የመሀል ከተማ የእርስበርስ የመኖር፤ የመረዳዳት እና አጠቃላይ መስተጋብሩ መሸርሸር ከጀመረ ቆይቷል፡፡ አሁን በይበልጥ የአዲስ አበባ ነዋሪ ከመሀል ከተማዉ ርቀዉ ባሉ የኮንዶሚኒየም ቤቶች ህይወትን ‘ሀ’ ብሎ ይጀምራል፡፡ አዲስ በሚኖርበት አካባቢ ካለዉ ህብረተሰብ ጋር ተቀባይነትን አግኝቶና ተላምዶ ለመኖር ፈተናዉን መጋፈጥ ግድ ይላል፡፡ አዲስአበባ ዙሪያ የሚገኙ አርሶአደሮች ተገቢዉ ካሣ ሳይከፈላቸዉ እና
የሚገባቸዉ ጥቅም ሳይጠበቅላቸዉ በጋራ መኖሪያቤቶች ፕሮጀክት ሳቢያ እንግልት እንደደረሰባቸዉ ይታወቃል፡፡ ይህ የሆነዉ ግን በመንግስት መዋቅሩ ዝርክርክ፤ አድሏዊና ገፊ አሰራር እንጂ መሀል ከተማዉን ጥሎ በሚሄደዉ የአዲስ አበባ ነዋሪ አይደለም፡፡ በዚህ ሳቢያየአዲስ አበባ ነዋሪ በሁለት ስለት ይወጋል፡፡ አንድም በገዛ አስተዳድሩ ሁለትም በሀሰተኛ የበዳይ ትርክት፡፡

ማህበራዊ ቀዉሶችን መቋቋም ያቃታቸዉ ዜጎች ለአእምሮ ጤና እክል ማለትም ለጭንቀት ለድባቴ ተጋላጭ መሆናቸዉ አይቀሬ ነዉ፡፡ ባስ ሲልም ራስን እስከማጥፋት የሚደርስ ከባድ ዉሳኔ በዉድ ህይወታቸዉ ላይ እንዲወስኑ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ከላይ ያነሳኋቸዉን የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ቀዉሶችን ስታስቡ አንድ ትልቅ ምስል አእምሯችሁ ዉስጥ መከሰቱን እገምታለሁ፡፡ ድህነት! ቅጥ ያጣ ድህነት እጣፈንታዉ የሆነ ህብረተሠብ ይኖረናል፡፡ እንግዲህ አነዚህ ቀዉሶች ተዳምረዉ፤ መፍትሄ ሳያገኙ ቀርተዉ ልካቸዉን ሲያልፉ ወደ ፖለቲካዊ ቀዉሶች ይሸጋገራሉ፡፡ የፒራሚዱ የላይኛዉ ክፍል ማለት ነዉ

Daron Acemoglu & James A. Robinson

Economic growth and prosperity are associated with inclusive economic and political institutions, while extractive institutions typically lead to stagnation and poverty

አጫጭር ሀሳቦች እንደመፍትሔ

አዲስአበባ ዉስጥ የመኖሪያ ቤት ጉዳይ እንዲሁም በአገር ደረጃ ደግሞ የመሬት ጉዳይ እጅግ ጥንቃቄ የሚሻ በመሆኑ የመንግስት ፖሊሲም እነዚህን ጉዳዮች በልዩ ትኩረት እና የአመራር ጥበብ ሊይዝ ይገባል፡፡ ህገ-ወጥነትንም ችላ ሳይል መቆጣጠር አለበት፡፡ የፍትህ ተቋማትም ከህዝቡ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በሚገባ በመመርመር ፍትህን ማስፈን ይጠበቅባቸዋል፡፡ የአዲስአበባ ነዋሪ ተገቢዉን ዉክልና እንዲያገኝ መሰራት አለበት፡፡ መንግስትም ለ አድልዎ የተጋለጡ አሰራሮችን በማስወገድ ሁሉም ዜጎች በእኩል ተወዳዳሪ የሚሆኑበትን ስርአት መዘርጋት ይጠበቅበታል፡፡አካታች የሆኑ ተቋማት (Inclusive Institutions) ሊኖሩን ግድ ይላል፡፡

በህጋዊ አግባብ የተመዘገቡ እና ካላቸዉ ላይ በመቀነስ እየቆጠቡ የመኖሪያ ቤት ባለቤት ለመሆን የሚጠባበቁ ዜጎች እጅግ ብዙ ከመሆናቸዉ አንጻር የተሻሻሉ የቴክኖሎጂ አማራጮች ያሉበት ዘመናዊና ቶሎ መጠናቀቅ የሚችሉ ቤቶችን የዉጭ የግንባታ ተቋራጮችን ጭምር ተሳታፊ በማድረግ ቤቶች እንዲጠናቀቁና ያልተጀመሩም በአፋጣኝ እንዲገነቡ አቅጣጫ መሰጠት ይኖርበታል፡፡ መንግስት ገና ሊሰራቸዉ ካሰበዉ እና ገንዘብ የሚሰበስብባቸዉን ፕሮጀክቶች ያዝ በማድረግ አንገብጋቢ ወደሆነዉ ፕሮጀክት ፊቱን በማዞር የዜጎቹን የአመታት ጥያቄ መልስ መስጠት ይገባዋል፡፡

ጉዳዩ የሚያንገበግባችሁ ዉድ የከተማዬ ነዋሪዎች በሙሉ

ከችግሩ ጥልቀት እና ዉስብስብነት አንጻር የተዳሰሰዉ በጣም ጥቂቱ ነዉ፡፡ በመሆኑም በቻልነዉ አቅም እንደ #ፍትህለአዲስአበባ  #JusticeForAddisAbeba ያሉ ዘመቻዎችን በመደገፍ ተጨባጭ ለዉጥ እንዲመጣ ልንረባረብ ይገባል እላለሁ፡፡ ‘‘ ፍትሐዊ ተጠቃሚነቷ የተረጋገጠባት አዲስ አበባ ለሁላችን ትበቃለች! ’’ የሚለዉ የአዲሱ ዓመት መልዕክቴ ነዉ፡፡ መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን!

(አህመድ መሐመድ፡ ጷግሜ 2012፡ አዲስ አበባ)

Related Posts