ለልማት የሚነሱ ሰዎች ወዴት ነው የሚሄዱት? እንዴትስ ነው የሚኖሩት? አሁን እንዴት ናቸው? የአንድ መንደር ነዋሪዎች ቅንጭብ ታሪክ

አዲስ አበባ-ሠፈረ ሰላም፣ ለቡ ተገጣጣሚ

የዛሬ አስራ ሁለት ዓመት ተወልደን ያደግንበት ሠፈረ ሰላም/ወላሞ ሰፈር የተወሰነ ቦታ ለመንገድ ስራ (ለልማት) ይፈለጋል እና መፍረስ አለበት ተባለ። መንገዱ የሚነካቸው የመንግስት (የቀበሌ) እና የግለሰብ ቤቶች በስማቸው የተመዘገቡ ሰዎች ለስብሰባ ተጠሩ። መኖሪያ ቤቶቻቸው ያረፉባቸው ቦታዎች ለልማት እንደሚፈለጉ እና እንደሚፈርሱ ለባለቀበሌ ቤቶቹ በምትኩ ሌላ የቀበሌ ቤት ለባለግልቤቶቹ ደግሞ ካሳ እንደሚሰጣቸው ተነገራቸው። ቤቶቹ በነሱ ስም ስለተመዘገቡ ስብሰባው ላይ የተገኙት በብዛት ወላጆቻችን ነበሩ። ስለዚህ የስብሰባውን ሙሉ ይዘት ለመዘርዘር አልችልም። ነገር ግን ተሰብሳቢዎቹ በቀረበላቸው አማራጮች ደስተኛ እንዳልነበሩና ተደጋጋሚ ስብሰባዎች ተደርገው እንደነበር አስታውሳለሁ።

የእኛ ቤት እና አብረው ተያይዘው የነበሩት ሁለት ተጨማሪ የቀበሌ ቤቶች፣ ከላይ ሰፈር እና ከፊት ለፊታችን ካሉት የግል ቤቶች ጋር ተያይዘው የነበሩ ሌሎች አራት የቀበሌ ቤቶች እንደሚፈርሱ እና ነዋሪዎቹም እንዳሉ በጊዜያዊነት ወደ ተዘጋጁት ለቡ ተገጣጣሚ ቤቶች መግባት እንዳለብን ተወሰነ። ለቡ በግዚያዊነት ተዘግጅተዋል የተባሉትን መጠለያዎች አስጎበኟቸው። ከነበርንበት ሰፈር አንፃር ለከተማ በጣም ሩቅ፣ መንገድ የሌለው፣ በጭቃ የተጨመላለቀ፣ ከተራራ ስር የተሰሩ ጠባባብ ተገጣጣሚ መጠለያዎች ነበሩ። እንዴት ሆነን እዛ እንደምንኖር በወቅቱ የማይታሰብ ነበር። አባቴ እንደነገረኝ መጀመሪያ መጠለያዎቹ ታስበው የተሰሩት ለወታደሮች ነበር። ወታደሮቹ «እኛ ዶሮ አይደለንም እዚህ ውስጥ ቤተሰብ ይዘን የምንገባው» ብለው እምቢ አሉ።

የባለግል ቤቶቹ ከቀበሌ አስተዳዳሪዎች ጋር በካሳ ጉዳይ ተደራድረው እስኪጨርሱና ቤቶቹ መፍረስ እስኪጀምሩ እዛው ቆየን።በስተመጨረሻ ግን አይቀር ሆነና የማፍረስ ስራ ተጀመረ። ከባለ ግልቤቶቹ ጋር በምን እንደተስማሙ እኔንጃ ብቻ የማፍረሱ ነገር ቁርጥ ሆኖ አንድ ቀን በጠዋት ትልልቅ አፍራሽ መኪኖች ሰፈራችንን ወረሩት።እቃዎቻችንን በአስቸኳይ ጭነን መውጣት ግድ ሆነብን። የዛን ቀን የነበረው ስሜት አሁን ይሄን ስጽፍ እራሱ እየተሰማኝ እጄ ይንቀጠቀጣል።እዛው ሰፈር የሚቀሩት የሰፈር ሰዎች ግልብጥ ብለው ወጡ። ዕቃ መጫኛ መኪናዎች ተደረደሩ። ግማሹ ያለቅሳል ግማሹ አይዟችሁ ይላል ግማሹ ዕቃዎችቻችንን ይጭናል። ሰፈሩ ድብልቅልቁ ወጣ። ያን ቀን በማላስታውሰው ምክንያት ቤቶቹ ሳይፈርሱ ቀሩ፤ ዕቃዎቻችን እና ጥቂት ሰዎች ግን ወደ ለቡ ሄድን።

ያኔ ሁለት እናት እና ልጅ የሆኑ ድመቶች ነበሩኝ። ልጅየውን እንደምንም በቦርሳ ደባብቄ ከዕቃ ጋር ተጭነን ይዤው ሄድኩ። እናቱ ግን ጠፍታ ልናገኛት ስላልቻልን አባቴ እሷን ሊፈልግ የዛን ቀን እዛው አደረ። አንድ ጎረቤታችን (ሁሌ ማታ ማታ ተሰብስበን ቡና የምንጠጣበት ቤት) የተወሰኑ ዕቃዎችና አልጋ አስቀርተው እዛው ሰፈር ግማሾቹ ልጆች አደሩ። የተቀረነው ከዕቃ ጋር ተጭነን ወደ ለቡ ተገጣጣሚ ቤቶች ተወሰድን።በንጋታው አመሻሽ ላይ ከስራና ትምህርት በኋላ ሳንጠራራ ሁላችንም የድሮ ሰፈር ተገኘን። አባቴ ድመቷ ከዛፍ ላይ እንደተገኘችና ለሊቱን ሙሉ ስትጮህ እንዳደረች ነገረን። እኛም በጅቦች ጩኸትና ጨለማ ተከበን ማደራችንን ነገርነው።ሁላችንም ዛሬ እዚህ ካላደርን አልን። ጎረቤት ተሰብስበን ቡና እየጠጣን ብዙ ምሬቶች አወራን። ማፍረሱ ተጀምሮ የነሱ ቤት እስካልተነካ ድረስ እዚህ ነው የምናድረው ተባባልን።

አባቴ በንጋታው ድመቷን እና ቀሪ ዕቅዎቹን ጭኖ ሄደ። እኛ (በብዛት ስራ እና ትምህርት ያለን ወጣቶች) ቀን ቀን ስራ እና ትምህርት ላይ እየዋልን ማታ ማታ እዛው ሰፈር እየሄድን እናድር ነበር።ለቡ የተዘጋጁት ተገጣጣሚ ቤቶች ለኛ (ከሰፈረ ሰላም ለሄድነው ሰባት ቤተሰቦች) ብቻ የተዘጋጁ አልነበሩም። አቀማመጣቸው ልክ እንደ አንድ መጠነኛ አዳራሽ ሆኖ ውስጡ ለስድስት የተከፋፈለ ነው። እነዛ ስድስቶቹ ደግሞ ውስጣቸው በግማሽ ለሁለት ተከፍሎ ሁለት ክፍል እንዲሆን ተደርገዋል። እነዛ ስድስቱ ለስድስት ቤተሰብ የተደለደሉ ናቸው።

ልክ እንደኛ ከቄራ፣ አራት ኪሎ እና ከሌሎች ሰፈሮች ተነስተው የነበሩ ቤተሰቦችም እዛ እንዲሰፍሩ እየተደረገ ነበር። ከአንድ ሰፈር የመጣነው ቅርብ ለቅርብ ከነበርን ጎረቤቶች ሌላ ሦስት ቤተሰቦችም ትንሽ ቆይተው ተቀላቀሉን።መጀመሪያ ጭር ያለ የነበረው ሰፈር (በቃ ሰፈር ልበለው) ቀስ በቀስ ከተለያዩ የአዲስ አበባ አካባቢዎች ተነስተው በመጡ ሰዎች መሞላት ጀመረ።ከዛ ሰፈር ወጥቶ ወደ ስራ እና ትምህርት ቤቶች መሄድ እና ተመልሶ መግባት አድቬንቸር መሆን ጀመረ። አሁን ድምቅ ብሎ ለቡ መብራት ዋና የትራንስፓርቶች መዳረሻ ሳይሆን በፊት ወደ ለቡ የሚገባው ጋሪ ብቻ ነበር። በተለይ ወደ ውስጥ ወደ ተገጣጣሚማ አይገባም። በጣም ጭቃ ነበር ደግሞም ጨለማ። ወይ መዚቃ ቤት የሚባለው ድረስ ሄደን ጥቂት የግል ቤቶች መሰራት እየጀመሩ ስለነበር የእነሱን መብራት ተገን አድርገን እንገባለን እንጂ።ማታ ማታ ሳንደዋወል ማን ገባ ማን ቀረ ሳንባባል አንገባም። ወንዶቹ በተለይ እኛ ሴቶቹ መግባታችንን ሳያረጋግጡ አይገቡም ነበር። ሌላ እስኪስተካከል እና ለጊዜው ነው ስለተባልን በተስፋ ስድስት ወር ለመኖር።

በነዛ ስድስት ወሮች ውስጥ የተፈጠረ ግን ምንም አዲስ ነገር አልነበረም። እኛ ግን የስድስት ቤተሰቦችን ድምጾች (ቲቪ፣ ራዲዮ፣ ጭቅጭቅ፣ የስልክ ወሬ. . .) እየሰማን በሰላም መተኛትን ቻልንበት። የተሰራው የህዝብ ሽንት ቤትም ፊት ለፊታችን ስለነበር ሰው ሲገባና ነፃ ሲሆን የሚሰማውን ድምፅ በመገመት ማወቅ ቻልን።ስድስት ወሩ ዓመት ዓመቱ ሁለት ዓመት ሆነ ግን ምንም የለም። ጭራሽ ለቡ አዲስ ቀበሌ ተሰርቶ ከድሮ ሰፈር ፋይላችንን እያዛወርን አዲስ የነዋሪነት መታወቂያ እንድናወጣ ተደረገ። በየመሀሉ የተለያዩ ተስፋ የሚሰጡ ወሬዎችን (ኮንዶሚንየም ይሰጣችኋል ቁጠባ ጀምሩ አይነት) ብንሰማም ምንም ግን የሚሆን ነገር አልነበረም። እኛም ቀስ በቀስ መደላደል ጀመርን። የጋራ ሽንት መፀዳጃዎች ማስመጠጥ፣ ቦኖዎች ማስከፈት፣ ትንንሽ አጥሮች ማጠር ጀመርን። ጉልቶችም ተጀመሩ። ስንቱ በድሮ ሰፈሩ ገንብቶት የነበረውን መተዳደሪያ እንዳጣ ቤቱ ይቁጠረው።

ተገጣጣሚ ቤት

ይህ በእንዲህ እንዳለ እኔ ለትምህርት ከሁለት ዓመት የተገጣጣሚ ኑሮ በኋላ ከሀገር ወጣሁ። በደወልኩ ቁጥር ግን ምን አዲስ ነገር እለ እያልኩ እጠይቅ ነበር። የሰፈሩ ሰው ተስማምቶ ዕድር ጀምሯል፣ ትንንሽ ቢዝነሶች (ጉልቶች) እየበዙ ነው ከሚል ሌላ የምትክ ቤት የሚባል ወሬ ተረሳ። ከሶስት ዓመት በኋላ ወደ ቤት ስመለስ ሰፈሩ ሞልቶ ትራንስፓርትም ተሻሽሎ አገኘሁት። አዳዲስ የግል ቤቶችም ሰፈሩን ሞልተውት ነበር::

ያለው የጋራ መፀዳጃ አርጅቶ ቆርቆሮው ተበጣጥሶ ቶሎ ቶሎ እየሞላ እንደሚያስቸግርና ከቤቶቹ መሀል እንደመሆኑ ሽታው ጉንፋን እንደሚይዛቸው ስለምሰማ ፤ ተማሪ እያለሁ ስራ እሰራ ስለነበር ብር አጠራቅሜ ለአዲሱ ሰፈራችን የጋራ መታጠቢያ እና መፀዳጃ ቤት ለመስራት አቅጄ ነበር። የመጣሁት ለአንድ ወር ስለነበር ወዲያው ለሰፈር ልጆች ሐሳቤን ነገርኳቸው። በቃ እዚሁ መኖራችን ላልቀረ በቻልነው መጠን አንድ አንድ ነገሮችን እንድናሻሽል ተስማማን። ለሦስት ቀበሌዎች ደብዳቤ ፅፈን ሄድን። መጀመሪያ ሐሳባችን እንግዳ ሆነባቸው። ደብዳቤው የጋራ መታጠቢያና መፀዳጃ ቤት እንድንሰራ እንዲፈቅዱልን እና እንዲያግዙን የሚጠይቅ ነበር። ከሀላፊ ሀላፊ ሲያሽከረክሩን ቀናት አቃጥለው ከዛ ከነዋሪው ፊርማ አሰባስቡ አሉን። በፍጥነት ፊርማዎች አሰባሰብን። ወረቀቱን ይዘን ሌላ ቀን ሄድን። ተቀበሉን ከዛም መልሱን እየተመላለሳችሁ ጠይቁ ተባልን።

እኔ ተመልሼ እስክሄድ ባይሆን እንዲጀመር ስለፈለግኩ በቀበሌው ባለፍኩ ቁጥር እጠይቅ ነበር። አሁን በአዲስ ቁጥባ ባንክ ቁጥር ከፍታችሁ 25,000 ብር አስገቡና ወረቀት አምጡ እስከዛ ስለ ውሀው ፍሳሽና ሌሎች ነገሮችን በተመለከተ ከግንባታ ክፍሎች ጋር ተነጋግረን እንጠብቃችኋለን ተባልን። ደስ አለን። እኔም የሚያስፈልገውን ገንዘብ አስቀምጬ ጉዳዩን ለሁለት ታታሪ ልጆች አደራ ሰጥቼ ወደ ውጭ ተመለስኩ።እየደወልኩ በጠየቅኩ ቁጥር ተስፋ የማይሰጥ ነገር ነው የምሰማው። አንዴ መጥተው ቦታውን የሚያዩት የሉም፣ አንዴ ውሀ ልማት፣ አንዴ ጅኒጃንካ እያሉ ተስፋችንን አጨለሙት። ከተወሰነ ግዜ በኋላ ግን ድንገት ቀበሌው እራሱ ግንባታ ጀመረ። የእርዳታ ድርጅት ብር ሰጥቶ ስለ ነበር ነው ተብለው ቢታሙም እሰይ! አዲስ ተስፋ ብለን ተቀበልን። ከዛ በኋላ በዓመት አንዴም ሁለቴም ስመለስ ባይ ባይ የተገነባው የመታጠቢያ ቤት አገልግሎት መስጠት አይጀምርም። ምክንያቱ? አይታወቅም።

ሰዉ ግን ሰፈሩን አረንጓዴ እያደረገ የራሱን ትንንሽ ውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ያላቸው ግቢዎች ፈጥሮ ነበር። የኅብረት ሱቆች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ወፍጮ ቤትች፣ መጠጥ ቤቶች፣ ወዘተ በዙሪያው ተስፋፍተው ደምበኛ ሰፈር ሆነ። አንዴ ቀበሌዎች ጠርተው «የቀጠላችሁትን አፍርሱ አሉን» አለ አባቴ፤ ግን እንዴ እኛ የቤተሰብ ቁጥር እየጨመረብን እዚሁ ቋሚ ኑሮ እየኖርን የግድ ቦታ ያስፈልገናል ብለው ተከራከሩ። ሳያፈርሱ ቀረ።

ኦ! በነገራችን ላይ፥ ኩሽናም የጋራ ነው።

እኔ፣ዋልያ ቢራ እና ...

ይኸው ለቡ ዛሬ አካባቢው ያሉ ቤቶች በብዙዙዙ ሚሊዬን የሚሸጡበት ልጥጥ ሰፈር ሆኗል። ተገጣጣሚ ቤቶቹም ነዋሪዎቿም አሉ። ቤቶቹ የሰፈሩበት ቦታ ሲለካ ነበር ምን ሊያደርጉት እንዳሰቡ እንጃ ሰሞኑን ደሞ የቤት ኪራይም እንቀበልም ሰዎቹ ለስልጠና ናዝሬት ሄደዋል እየተባሉ ነው። ከ60 በላይ የሚሆን ቤተሰብ መጪውን ሳያቅ ቁጭ ብሏል — ይኸው 12 ዓመት….

(ከድሮ ሰፈር አብረን ከመጣነው ውስጥ ሦስት ሰዎች አርፈዋል።)

Related Posts