ፍትሕ ለአዲስ አበባ

ፍትሐዊ ተጠቃሚነቷ የተረጋገጠባት ከተማ ለሁላችን ትበቃለች!

ፍትሕ ለአዲስ አበባ

ታማኝነት ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት

አላማዎች

አዲስ አበባ እና ነዋሪዎቿ ባለፉት አስርት አመታት ከአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ ፥ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እሴቶች ላይ ተቋዳሽ ከመሆን ይልቅ ስርአቶች በፈጠሩበት መገፋት በፖለቲካዊ ውክልናም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ላይ ተገላይ ማህበረሰብ የተደረገ ሲሆን ከዚህም ባለፈ ህጋዊ ውክልናን በህግ ማእቀፍ እንዲያጣ ተደርጓል። እኛ ሁሉም የኢትዮጵያ ዜጎች ከአገሪቷ ሁለንተናዊ በረከቶች እኩል ተቋዳሽ ሊሆኑ ይገባል ብለን እንደማመናችን ከተማችን አዲስ አበባም ሆነች የአዲስ አበባ ነዋሪ እነዚህ ሶስት መሰረታዊ ፍላጎቶቹ እስኪረጋገጡለት ድረስ አበክረን እንታገላለን።

ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ እና ተጠቃሚነት

በከተማዋ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ የመጣው ስር የሰደደ ድህነት የመሰረተ ልማት አቅርቦት እጥረት ፥ የስራ አጥነት ችግር እና በቤቶች ልማት ፕሮጀክቶች ላይ እና በሌሎች ዘርፈ ብዙ ቢሮክራሲያዎ በደሎች
በከተማው ነዋሪ ላይ ሲፈፀሙ የኖሩ ሲሆን እነዚህ በደሎች በዘላቂነት የሚፈቱበት መንገድ እንዲፈጠር ነዋሪዎቿን ማስተባበር ፥ብሎም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ማድረግ!

ማህበራዊ ምስቅልቅሎችን ቀንሰው ማየት

አዲስ አበባ ላይ የተከሰቱ ችግሮች በከተማዉ ነዋሪዎች መካከል ማህበረሰባዊ መስተጋብሮችን ተቃርኖ ላይ የጣሉት ሲሆን ፥ ሌላው ደግሞ ነዉሪዎቿ በዙሪያዋ ካሉ ወንድም ህዝቦች ጋር በጠላትነት እንዲተያዩ የሚያደርጉ የመንግስት ፕሮጀክቶች መፍትሄ እንዲፈጠርላቸው መስራት ፥ ብሎም በከተማዋ ውስጥ ለልማት በሚል የሚፈናቀሉ ከተማዋን ያቀኑ ነዋሪዎች ባይተዋር እንዲሆኑ እና ማህበራዊ መስተጋብራቸውም እንዲናድ መደረጉ ተገቢነት እንደሌለው በማመን ወደፊትም እንዲህ አይነት የከፉ በደሎች እንዳይፈፀሙ መታገል።

 

የወጣቶች ተስፋ

የከተማዋ ነዋሪዎች/ወጣቶች በከተማቸው ፥ ብሎም በአገራቸው ላይ የባለቤትነት ስሜትን እንዲያዳብሩ እና ከሌሎች የአገራቸው ወጣት ነዋሪዎች ጋር ወንድማማች ስሜት እንዲኖራቸው ፥ በኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውም ለወገናቸው ብሎም ለአገራቸው የራሳቸውን ጉልህ ድርሻ የሚያበረክቱበት መድረክ እንዲመቻች ፥ ተስፋቸውን ተነጥቀው የነበሩ ወጣቶች ተስፋቸው የሚለመልምበትን መንገድ መክፈት

ራዕያችን

  • በአዲስ አበቤያዊ ስነ-ልቦና የተዋቀረ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ፍላጎት የሚያስጠብቅ ፣
  • በከተማዉ ጉዳይ ላይ ጠያቂ እና ምክንያታዊ ትዉልድ እንዲፈጠር የሚያግዝ፣
  • የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነታቸዉ ዋስትና የሚያገኝበት ፍትሐዊ መደላድል እንዲኖር የሚሰራ፣
  • አዲስ አበቤዉ መብትና ግዴታዉን አዉቆ አንዲንቀሳቀስ የሚያስተባብር፣
  • በከተማዋም ይሁን በፌደራላዊ የመንግስት መዋቅሮች ዉስጥ አዲስ አበቤዉ እዉነተኛ ተወካይ እንዲኖረዉ የሚያስችል፣
  • በማናቸዉም ከተማዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከሌሎች የሀገሬዉ ወንድም እና እህት ህዝቦች ጋር እኩል ተሳትፎ እንዲኖረዉ የሚተጋ፣
  • የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ለከተማቸዉ እና ለሀገራቸዉ እድገት የበኩላቸዉን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የሚያበረታታ፣
  • መንግስታት እና አስተዳዳሪዎች ቢቀያየሩም ዘመን ተሻጋሪ የሆነ የአዲስ አበቤዉ አለኝታ የሆነ ተቋማዊ አሰራር የተዘረጋበት፣
  • ከብሔርተኝነት፣ ሐይማኖታዊ እና ፖለቲካዊ አስተሳሰቦች ነጻ የሆነ የሲቪክ ማህበር ማቋቋም፡፡

መጣጥፎች እና ወቅታዊ ጉዳዮች

26 Oct: የዛሬ አበባዎች የነገ ……… ?

እኛ የአዲስ አበባ ወጣቶች ትናንት የተመኘነዉን ብሩህ ተስፋ ባንደርስበትም፤ ወጣቱ የሚጠይቀዉን መሠረታዊ ጥያቄዎች ግን ለሚመለከተዉ አካል ለማስተላለፍ ግን ደርሰናል፡፡ ‹‹ለምን?›› እንላለን፡፡ የዛሬዎቹ ‹‹አበቦችም›› የነጋቸዉን መልካም ፍሬ እንዲያመልጣቸዉ አንፈቅድም፡፡ ሀገራችንም ዛሬ ላይ ብዙ የደረሱ የትናንት አበቦች ስላሏት ምናልባት ለመልሱ ብዙ አንርቅ ይሆናል።

11 Oct: 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የማን ናቸው?

‘ይህ ለቤት መግዣ አላማ የሚሆን ዝግ የቁጠባ ሂሳብ ነው’ ይላል በ40/60 የቤት ባለቤት ለመሆን ከንግድ ባንክ ጋር ውል ፈፅመው የሚገባውን ገንዘብ ገቢ የሚያደርጉበት የቁጠባ ደብተር፡፡ ውሉን ፈፅመው ገንዘባቸውን ያስገቡ እና በየወሩ የተለያየ ቀዳዳዎችን በሕይወታቸው እየተዉ ነገን ተስፋ በማድረግ የቆጠቡ ነዋሪዎች በ2011 ድንገተኛ የመመሪያ ለውጥ በምክትል ከንቲባው ተደረገ፡፡

ባቡር ጣቢያ

ዘመቻዎች

በአዲስ አበባ የታየውን የመሬትና የኮንዶምንየም ምዝበራ በመቃወምና ፍትህ ለመጠየቅ የተዘጋጀ የማህበራዊ ሚድያ ዘመቻ።

በአዲስ አበባ የሚስተዋለውን የነዋሪዎች ቤት አልባነት ለመቅረፍ ከ1997 ጀምሮ ተመዝግበው በየወሩ ሲቆጥቡ የነበሩ የነበሩ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቤት ሳዯገኙ ቀርተው ኢፍትሃዊ በሆነ አሰራር በቆጠቡት ገንዘብ የተሰራውን የጋራ መኖሪያ ቤት ላልተመዘገቡና ላልቆጠቡ ግለሰቦች መዘዋወራቸው ቁጣን ቀስቅሷል። ይህንን በመቃው የታየው አይን ያወጣ ሙስናና ምዝበራ እርምት እንዲወሰድበት፤ አጥፊዎች አንዲጠየቁ እንዲሁም ፍትህ ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች የሚጠይቅ የማህበራዊ የተቀናጀ ዘመቻ ሀሙስ ነሀሴ 28/12/1ዓ.ም & አርብ 29/12/2012ዓ.ም በዋናነት ትዊተር ላይ አካሂደን ነበር

በዋናነት እነዚህን #ፍትህለአዲስአበባ #አዲስአበባ #ኢትዮጵያ #JusticeforAddisAbeba #AddisAbeba #Ethiopia ሃሽታጎች ተጠቅመናል። መልእክቶቻችን እንዲደርሳቸው በትዊተር የሚገኙ የመንግስት ሃላፊዎችን እና ተቋማትን እንደ @TakeleUma @DanielBekele @AdanechAbiebie  @ashenafi_meaza @BilleneSeyoum @FAGEthiopia @MoP_Ethiopia @PMEthiopia @dagmawit_moges እንዲሁም መገናኛ ብዙኃንን @shegerfm  @VOAAmharic @Wazemaradio @dw_amharic ጠቅሰናል።

ስለዘመቻው ማብራሪያ በአማርኛ እና በእንግሊዘኛ ይሄን -> ሊንክ በመከተል ማግኘት ይቻላል

ተሳትፎ

ማንኛውም የአዲስ አበባ ጉዳይ የሚመለከተው በቀጥታ በፍትሕ ለአዲስ አበባ አንቅስቃሴ ላይ ለመሳተፍ የሚፈልግ፣ እውቅቱን ለማካፈል የሚሻ፣ ጠቃሚ መረጃ ያለው ይህን መልእክት መላኪያ ፎርም በመጠቀም ሊያገኝን ይችላል። በተጨማሪም ኢንተርኔት እና ጋዜጦችን ለማያገኙ ነዋሪዎች እዚህ ላይ የቀረቡትን መረጃዎች በማተም እና በማድረስ እንድትተባበሩን በአክብሮት እንጠይቃለን።